
“ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እንደዚህ ያደረገ ብቻዬን ቢያገኘኝ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” መምህርት ፍሬሕይወት አሰፋ
ፍሬሕይወት አሰፋ በሙያዋ መምህርት ስትሆን የሃያ ስድስት አመት ወጣት ናት። ወጣቷ ከፒያሳ መካኒሳ በመመላለስ የዕለት ከዕለት ሥራዋን አከናውና ትመለሳለች።
ፍሬሕይወት ከወጭ አንጻር የብዙኃን የሕዝብ ማጓጓዣ መጠቀም ምርጫዋ ቢሆንም በወንዶች በሚደርሱባት ፆታዊ ትንኮሳዎች የተነሳ ግዴታ ካልሆነ በስተቀር መጠቀም ማቆሟን ለኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (ኢትመባሴማ) ተናግራለች። “ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እንደዚህ ያደረገ ብቻዬን ቢያገኘኝ ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ብዬ አስባለሁ” ስትል በምሬት አንድ አጋጣሚዋን ታስታውሳለች።
ነገሩ እንዲህ ነው። ከአያት ወደ መገናኛ በከተማ አውቶቡስ ስትጓዝ አውቶቡሱ በመሙላቱ ቆማ ለመሄድ ትገደዳለች። በጉዞዋ ላይ አንድ ወጣት ምቾት በማይሰጥ ሁኔታ ሲጠጋት እና ሲነካት እንደነበር የምታስታውሰው ወጣቷ “ብዙ ጊዜ ከሚያጋጥሙኝ ይሄኛው ከባዱ ነበር” ትላለች።
“በሰዓቱ ሥርዓት እንዲይዝ ሰው እየሰማ ጮክ ብዬ ተቆጥቼ ተናገርኩት” ስትል ፊቷ ላይ መማረሯ እየታየ ታብራራለች። ብዙ ሴቶች አማራጭ በማጣት እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳ ችለው እንደሚያልፉ ከጓደኞቼ ገጠመኞችም ሆነ ከራሴ አጋጣሚዎች ተረድቻለሁ” ትላለች።
የሕዝብ መጓጓዣ በተለይም የከተማ አውቶቡስ፣ ሃይገር እና በተለምዶ ቅጥቅጥ ተብለው የሚጠሩት ሎንችናዎች በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰአት ላይ መያዝ ካለባቸው አቅም በላይ ተሳፋሪዎች ሞልተው ይሄዳሉ። የቸኮለ በጊዜ ወደ ቤቱ ለመግባት አንድም ወደ ሥራ ለመሄድ ሌላውም የግል ጉዳዮቹን ለመጨረስ ለመሳፈር የሚደረገውን ግፊያ ተቋቁሞ ከተሳፈረ በኋላ እንደ ክብሪት ተጠጋግቶ ቁሞ መጓዝ ግድ ይሆንበታል።
ይሄ ተጠጋግቶና ቆሞ መጓዝ በተለይም ለሴቶች ሌላ ችግር ይዞ ብቅ ይላል። ህገ ወጥ የአካል ንክኪ ፈልገው በሚገቡ ወንዶች ጥቃት ሲፈጸምባቸው ይታያል፤ ይደመጣልም።
ከዚህ በፊት የከተማ አውቶቡስ ተጠቃሚ የነበረችው እና መሰል ትንኮሳ ያጋጠማት ሸዋዬ ሙሉነህ “ከዛ ቀን በኋላ በባስ መሄድ አቆምኩ” ትላለች የደረሰባትን በማስታወስ። ወደ ሥራ ቦታዋ ለመድረስ ከቃሊቲ ወደ ቦሌ በመሄድ ላይ ሳለች በቆመችበት ልክ ያልሆነ ሙቀት ተሰማት።
በጣም ብዙ ሰው በመኖሩና ተጠጋግተው በመቆማቸው የምትሸሽበት ቦታ እንኳን አልነበረም። “ሰውዬው ከኋላዬ ነበር። ይተሻሸኛል። ባገኘሁት ክፍተት ለመራቅ ስሞክር ይከተለኛል።” ስትል በሰዓቱ የነበረውን ሁኔታ ትገልፃለች። “የሰውነቱ ወላፈን ይቀፋል፤ ደፍሬ እንዳልናገር ማን ያምነኛል? ትልቅ ሰው ነው። ስሜን ማጥፋትም መስሎ ታየኝ። ፌርማታ ደርሶ እስክወርድ በጣም ቸኮልኩ” ብላለች።
ሸዋዬ ስለዚህ ቀን ትናገር እንጂ ብዙ ጊዜ አጋጥሟት እንደሚያውቅ አልደበቀችም። “ሕዝብ መሀል ለማን አቤት እላለሁ?” ስትል በግድ የታክሲ ተጠቃሚ የሆነችበትን ሰበብ ትናገራለች።
በሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ በሴቶች ላይ የተለያየ ዓይነት መልክ ያላቸው ፆታዊ ጥቃቶች ይደርሳሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚና የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳዬ ስለ ፆታዊ ጥቃቶች ምንነት ሲገልጹ ከፍላጎት ውጪ ማነጋገር፣ ከሚገባው በላይ መጠጋት፣ ጠቀሳና የመሳም ምልክት ማሳየት፣ በአካል ላይ ከሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች ውስጥ እንደሚካተቱ አብራርተዋል።
በወንጀል ህጋችን አዋጅ ቁጥር 414/2004 የተለያዩ አንቀፆች ፆታዊ ትንኮሳዎችና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወንጀል መሆናቸውን በመደንገግ እንደየጥቃቶቹ ክብደት ቅጣታቸውን በማክበድ ያስቀምጣል ብለዋል። ነገር ግን ይሄው አዋጅ በልዩነት በሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ የሚደርሱ ወንጀሎች (ፆታዊ ትንኮሳዎች) በሚል አለመደንገጉን አክለዋል።
በተጨማሪም በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 602 ላይ ሴቶች በነፃነት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል የሚሉት ወ/ሮ ሰላማዊት ወንጀል ፈፃሚው የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ እና ስልጣኑን ካለአግባብ ተጠቅሞ ከሆነ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 407 መሠረት ከብዶ ይታይበታል ብለዋል።
በሌላ በኩል በህዝብ መጓጓዣ ውስጥ በሴቶች ላይ አንድ ግለሰብ ፆታዊ ጥቃቶችን (ትንኮሳዎችን) ከፈፀመ ለዚህ ተብሎ የተጻፈ የህግ ማዕቀፍ ባይኖርም በወንጀል ህግ እንዲሁም በወንጀል ሥነ ሥርዓት ህግ መሠረት እንደሚቀጣ አብራርተዋል።
ምንም እንኳን በህዝብ መጓጓዣ ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚደነግግ አዋጅ ወይም ህግ ባይኖርም ጥቃቶቹ በወንጀል ህጋችን እንደ ወንጀል እስከተዘረዘሩ ድረስ “ፆታዊ ትንኮሳውን የሚያደርሰው ግለሰብ በህጉ መሠረት ከመቀጣት እንደማያልፍ ኅብረተሰቡ አውቆ እንደዚህ አይነት ተግባር ከመፈፀም ሊቆጠብ ይገባል” ሲሉ ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚዋ አሳስበዋል።
በሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ የሚደርሱ ወንጀሎች እና ፆታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ትንኮሳዎችን በግልፅ የሚደነግግ አዋጅ እንዲረቅ እና እንዲፀድቅ በማድረግ በመጓጓዣ እጥረት ምክንያት ተጨናንቀው የሚጓዙና ለፆታዊ ጥቃት የሚጋለጡ ሴቶችን በጋራ በመሥራት ልንታድጋቸው ይገባል በማለት የህግ አውጭ አካላት፣ ሌሎች በውትወታ፣ በጥናት እና ምርምር ላይ የሚሰሩ ተቋማት የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ሴቶች ራሳቸውን እንዲያስከብሩና ተመሣሣይ ችግር ሲገጥማቸው እንዲተባበሩ፣ የህግ አካላት መፍትኄ እንዲያበጁ እንዲሁም አውቶቡሶች የሚጭኑትን የሰው ብዛት በመቀነስ መፍትኄ ቢሰጥ ስትል ጥቆማዋን ትሰጣለች።
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እየሰራ እንደሚገኝ ለማወቅ ወደ ድርጅቱ አምርተናል።
ብዛት ያላቸው አዳዲስ አውቶቡሶችን ወደ ሥራ በማስገባት እንዲሁም የተሳፋሪዎችን ቁጥር ከመነሻ ቦታዎች ላይ በመቀነስ 75 ሰዎችን ይዞ እንዲነሳ በማድረግ በአውቶብስ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ትንኮሳ ለመከላከል እየሠራ ነው ያሉን የድርጅቱ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ እንደሻው አለማየሁ ናቸው።
በተጨማሪም ድርጅቱ ከትኬት ቆራጭነት ጀምሮ እስከ አሽከርካሪነት ሴቶችን እያበቃ ነው ያሉ ሲሆን ከአሽከርካሪዎችም ሆነ ከተሳፋሪ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴቶች ለተቋሙ ቢያመለክቱ በአሽከርካሪው ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድና ተሳፋሪ ከሆነ ደግሞ ወደ ሕግ አካላት ለማቅረብ እገዛ ለማድረግ ድርጅቱ ፈቃደኛ ነው ብለዋል።