
ትንሽ ቆየት ብሏል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲን ሽልማት ያገኘ አንድ አጭር ዶኩ ድራማ ፊልም ተመልክቼ ነበር፡፡ ርዕሱ ሥራ የላትም ይላል። ፊልሙ የአንዲት ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች እናት የሆነችን ሴት የቀን ውሎ የሚያሳይ የአራት ደቂቃ ፊልም ነው።
ፊልሙ እናትየዋ ማለዳ ተነስታ የቤተሰቡን ቁርስ እና ምሳ ስታዘጋጅ፣ በጣም በፍጥነት የልጆቿን ምሳ ቋጥራ፣ ቤተሰቡን ቁርስ መግባና ቧላን ወደ ሥራ ልጆቿን ወደ ትምደህርት ቤት ሸኝታ፣ ለትምህርት ያልደረሰውን ልጇን ደግሞ አዝላ የቀረውን የቤት ሥራዋን ስታከናውን ያሳያል፡፡
ምሽት ላይም ባለቤቷ እራት የጋበዛቸው እንግዶች ስላሉ ልጆቿን ከትምህርት ቤት ለመቀበል ስትሄድ ለግብዣው የሚያስፈልጉትን ግብዐቶች ስትገዛዛ፣ ማታም እንግዶቹ እራት እየተመገቡ ከባለቤቷ ጋር ሲጨዋወቱ እሷ ቡና ስታፈላ እናያለን። አንደኛው እንግዳ ምግቡን አድንቆ ጋባዡን ባለቤቱ የት እንደምትሠራ ይጠይቀዋል። እንግዶቹ መሥርያ ቤቷን ለማወቅ በጓጓ ፊት መልሱን ሲጠብቁ ባል ትንሽ እንደመሳቀቅ ብሎ “ሥራ የላትም” በማለት ይመልሳል፡፡
ዋናው ጉዳይ እዚህ መልስ ላይ ነው። ከባል ቀድማ ከመኝታዋ ተነሥታ ሥራ የጀመረች ሴት የሥራ ቦታዋ ቤት ውስጥ ስለሆነ ብቻ ሥራ የላትም መባልዋ! በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከሥራ በማይቆጠሩ/ክፍያ በሌላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችና ክብካቤ ላይ ያሳልፋሉ፡፡ ሴቶች ጊዜያቸውን ምግብ በማዘጋጀት፣ ቤት በማጽዳት፣ ልጆችን፣ አረጋውያንን፣ የታመሙ ሰዎችን ወይም አካል ጉዳተኛ የቤተሰብ አባላትን በመንከባከብ ያሳልፋሉ። ገጠር የሚኖሩት ደግሞ ማገዶም ይለቅማሉ፤ ውሃም ይቀዳሉ፣ በግብርና ሥራ ላይም ተሰማርተው ይውላሉ።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ምንም እንኳን ወቅታዊ የሆነ ብሔራዊ የሰዓት አጠቃቀም መረጃ ባይኖርም በ2013 ዓ.ም. በማዕከላዊ ስታስቲክስ መሥርያ ቤት የተጠናቀረው ሪፖርት 34% የገጠር ሴቶች ማገዶ ለመልቀም ከ1-2 ሰአት እንዲህም 10% የሚሆኑት ደግሞ ከሁለት ሰአት በላይ መጓዝ አንደሚጠበቅባቸው ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ የመጠጥ ውሃ ክጉድጓድም ይሁን ከቦኖ ለመቅዳት 37% የሚሆኑት ሴቶች እስከ 2.5 ሰአት ይጓዛሉ። ሌሎች 15% ገደማ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ 3.5 ሰአት እንደሚጓዙ በማዕከላዊ ስታስቲክሱ ጥናት ተገልጿል፡፡
ከሥራ በማይቆጠሩ/ክፍያ በሌላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ጭምር እንደሚሰማሩ ‘ዕድገትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለሴቶች’ በሚል ርእስ በኦክስፋም የተዘጋጀ ሌላ ሰነድ ይጠቅሳል። ነገር ግን ከወንዶች በበለጠ ሴቶቹ በሶስት እጥፍ የቤት ውስጥ ክብካቤ ላይ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ይሄው ጥናት በዋቢነት የጠቀሰው የዩኤንዲፒ መረጃ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ሴቶችና ልጃገረዶች ለትምህርት፣ ለሥራና ለዕረፍት በቂ ጊዜ እንዳይኖራቸው ማድረጉን ጠቁሟል፡፡
ግለሰብ፣ ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውና ጊዜና ጉልበት የሚጠይቁትን ከሥራ የማይቆጠሩ/ክፍያ የሌላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች በማኅበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አይሰጣቸውም። ገቢ አይገኝበትምና ራሳቸው ይህን ሥራ ሲሰሩ የሚውሉትም ሆኑ ሌሎች የቤተሰብ አባላት እነዚህን ሴቶች እንደባለ ሥራ አይቆጥሯቸውም፤ የፖሊሲ ሰዎችም የነዚህን ሴቶች ልፋትና ጥረት ለሀገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋዖ ሰፍረው ቆጥረው አይመዘግቡም። ይህም በእነዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ከግምት ያስገቡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዳይቀየሱ ዕንቅፋት ሆኗል።
ዶክተር ላክስሚን ኮንተክስቹዋላይዝ አንፔይድ ኬር ኤንድ ውመን ኢምፓወርመንት በሚል ርዕሰ ባዘጋጀው ጥናት በርካታ ሴቶች በቤት ውስጥ ክብካቤ ሥራ ጊዜያዊ ርካታና ደስታ ቢያገኙም ከጊዜ በኋላ ግን የጤና እክል፣ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የመገለል ችግርና ራሳቸውን በሚፈለጉት የሙያ ዘርፍ እንዳያሳድጉና የሥራ ዕድል እንዳይኖራቸው እንቅፋት ሊሆንባቸው አንደሚችል ገልጿል። በተጨማሪም ችሎታቸውን በመገደብ የኢኮኖሚ ነጻነት እንዳይኖራቸው፣ በልጆቻቸው አስተዳደግ ላይም ጉልህ ሚና እንዳይጫወቱ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይም በጎ አስተዋጽዖ እንዳይኖራቸው ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
እነዚህን ጫናዎች ለመቀልበስ ከሥራ በማይቆጠሩ/ክፍያ በሌላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ሚዛናዊ ክፍፍልን ያዛቡትን ስር የሰደዱ ማኅበረሰባዊ ልማዶች መፈተሽና ወንዶችም ሴቶችም እኩል እንዲሳተፉባቸው ማድረግ አንዱ ስልት ነው። ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ የማኅበረሰብ ማኅበራዊ መዋቅሮችን፣ ትምሀርት ቤቶችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን በመጠቀም ወንዶች ከሥራ በማይቆጠሩ/ክፍያ በሌላቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ለመቀየር የግንዛቤ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አድካሚና ረጅም ጊዜ የሚወስዱትን ሥራዎች ጫና ለመቀነስ መሠረተ ልማቶችን በሟሟላት ሴቶችና ልጃገረዶች ለትምህርት፣ ለሥራና ለዕረፍት በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ማገዝ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ለማስፋት ፖሊሲዎችን መከለስና የመሳሰሉት ርምጃዎች መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉና ልምድ ያካበቱ ሀገራት ተሞከሮዎች ያሳያሉ። ለዚህም ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡